Posted on 2024-04-17 06:32:17
የሹዋሊድ ክብረ በዓል ሰላምን፣ አብሮነትን እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ ይከበራል፦ የሀረሪ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ከቀናት በኋላ የሚከበረው የዘንድሮው የሹዋሊድ ክብረ በዓልን በማስመልከት ከሀረሪ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተሰጠ መግለጫ፦ በዓሉ በሀረሪ ብሄረሰብ ዘንድ ለምዕተ አመታት ሲከበር የኖረና ከጥንት ጀምሮ በትውልድ ቅብብሎሽ ባህሉንና ወጎኑ ጠብቆ ዛሬ ላይ የደረሰ ባህላዊ በዓል ሲሆን በዓሉ ከሀረሪ ብሄረሰብ ባለፈ የመላው ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም አለም አቀፍ በዓል ነው። የሹዋሊድ በአል አከባበር የሀረሪ ህዝብ ልዩ መገለጫ እሴት ሲሆን የበዓሉ አከባበርም ሀገራችን ኳሏት ማራኪና የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው። የሹዋሊድ ክብረ በዓል ሀረር የምትታወቅበት የአብሮነት እሴትም ጎልቶ የሚታይበትና በከተማዋ የሚገኙ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ የሚያከብሩት ክብረ በአል ነው። የበዓሉ አከባበር የሀገራችን ሕዝቦች የአብሮነት ዕሴትን ከሚያጎለብቱ ባህላዊ በዓላት መካከል አንዱ ሲሆን በተለይም በምስራቁ የሀገራችን ክፍል የባህል ትውውቅ በመፍጠር የህዝብ ለህዝብ ትስስር በማጠናከር በኩልም ገንቢ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። የሹዋሊድ በዓል አከባበር በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከህዳር 25 / 2016 ጀምሮ የማይዳሰስ አለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህም ሐረር በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ሁለት ቅርሶችን በማስመዝገብ ብቸኛዋ የሀገራችን ከተማ አድርጓታል። የሹዋሊድ በተለይም የክልላችን ብሎም የሀገራችን የቱሪዝም ዘርፍ እንዲጎለብት ከማድረግ አንፃር የላቀ ጠቀሜታ ያለው በዓል ነው። ዘንድሮም የሚከበረው የሸዋል ኢድ በአል “ሸዋል ኢድ ለህብረ ብሔራዊ አንድነታችንና ለቱሪዝም እድገታችን” በሚል መሪ ሀሳብ በድምቀት ይከበራል። የዘንድሮው የሹዋሊድ በዓል አከባበርም ሰላምን፣ አብሮነትን እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል። በበዓሉም የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እና አጎራባች ክልሎች በሐረር ከተማ የባህል፣ ፌሲቲቫልና አውደ ርዕይ የሚካሄድ ሲሆን በበዓሉ ላይም ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎችና የአለም ሀገራት የሚመጡ እንግዶች ይታደሙበታል ተብሎ ይጠበቃል። የሀረሪ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚያዚያ 5 ቀን 2016 ዓ. ም ሐረር
Total visitors: 1120