Posted on 2024-04-21 20:51:22
በሀረር ከተማ ህዝብን ባለቤት ባደረገ መልኩ እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ:- አቶ ኦርዲን በድሪ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በሀረር ከተማ ህዝብን ባለቤት ባደረገ መልኩ እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለፁ። ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በከተማው በሚገኙ ወረዳዎች ባለፈው አንድ ወር በተከናወኑ ስራዎች ዙሪያ ለድጋፍና ክትትል ከተመደቡ አመራሮች ጋር ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱ ላይም በከተማው በሚገኙ ወረዳዎች የተከናወኑ ስራዎች በሚመለከት ሪፖርት ቀርቧል ። በውይይቱ ላይ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንዳሉት በከተማው ህዝብን ባሳተፈ መልኩ በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት ተገኝቷል። በተለይም በከተማው የአረንጓዴ ልማትና የከተማ ፅዳትና ውበት ስራዎች ለነዋሪዎቹ ምቹና በጎብኚዎች ተመራጭ ከተማ ለማድረግ እንደሚቻል ያመላከተ ነው ብለዋል። በጽዳትና ውበት፣በደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ፣በአረንጓዴ ልማት ስራዎች ፣ በህገ ወጥ ንግድና ግንባታ እና የመንገድ ዳር ጌጠኛ መብራቶች ስራዎች ዙሪ የተሰሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለበት ብለዋል። አመራሩ በቅንጅት በመስራቱ ውጤት ማምጣታቸውን ጠቅሰው በቀጣይም እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል። በቀጣይ በመደበኛነት ባለቤት ተቋማትና ወረዳዎች ህዝብን ባለቤት ባደረገ መልኩ በመንቀሳበስ ስራዎቹን ዘላቂ እንዲሆኑም በማድረግ ረገድ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል። በተለይም የጁገል አለም አቀፍ ቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ስራዎችም ተጠናክረው መቀጠል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
Total visitors: 1124