Posted on 2024-04-17 06:35:19
የሹዋሊድ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ የባህል ዐውደ ርዕይና ፌስቲቫል በሐረር ከተማ ተከፈተ የሹዋሊድ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ የባህል ዐውደ ርዕይና ፌስቲቫል በሐረር ከተማ ዛሬ ተከፈተ። የባህል ዐውደ ርዕዩና ፌስቲሻሉ የተከፈተው የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳና የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በተገኙበት ነው። እንዲሁም ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ አምባሳደሮች፣ የፌዴራልና የክልሉ የሥራ ሃላፊዎች፣ አባ ገዳዎችና ሌሎች እንግዶች በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል። በባህል ዐውደ ርዕዩና ፌስቲቫሉ አጎራባች ክልሎች እና የአርጎባ የባህል ቡድን እንዲሁም የባህል አልባሳትና ጌጣጌጥ አምራች ማህበራትና ተቋማት ተሳትፈዋል። የሸዋል ኢድ በዓልን አስመልክቶ የተዘጋጀው የባህል ዐውደ ርዕይና ፌስቲቫል የብሔር ብሔረሰቦችን ግንኙነት እንደሚያጠናክር የሐረሪ ክልል የባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ ሃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ ተናግረዋል። "ሸዋል ኢድ ለህብረ ብሔራዊ አንድነታችንና ለቱሪዝም እድገታችን" በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀው የባህል ዐውደ ርዕይና ፌስቲቫል ለሁለት ቀናት እንደሚቆይም አቶ ተወለዳ ተናግረዋል። በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) በዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡን የሚገልጽና ከዩኔስኮ የተሰጠ የሸዋል ኢድ የምስክር ወረቀት ቢል ቦርድ በክብር እንግዶቹ ተመርቋል። የሸዋል - ኢድ በዓል የኢድ አልፈጥር በዓል ከተከበረበት ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት ከተፆመ በኋላ ከስድተኛው ቀን ምሽት ጀምሮ እስከ ማግስቱ 10 ሰዓት ድረስ የሚከበር ነው። በዓሉ በሐረሪ ብሔረሰብ ወጣቶች ትኩረት የሚሰጠው እና በታዳሚው ዘንድ አብሮነትን እና ወንድማማችነትን እያጎለበተ የመጣ በዓል ነው።
Total visitors: 1119